የዳንኤል እይታዎች Daniel Kibret's views: ጩኸት እና ንግግር: በታክሲ እየሄድኩ ነው፡፡ መካከለኛው ወንበር ነው የተቀመጥኩት፡፡ አንዲት ሴትዮ በስልክ በንዴትያወራሉ፡፡ በጩኸታቸው መጨረሻ «እንዲያውም ካሁን በኋላ ካንተ ጋር መኖር አልችልም፤ በቃ»ብለው ዘጉት፡፡ በታክሲ ውስጥ የነበርነው ሁሉ በድንጋጤ እያየን ነበር ያዳመጥናቸው፡፡
ወዲያው አንዱ ቀልደኛ «እናቴ ይህንን በቃ የሚል ቃል እንኳን ቢተውት፤ ሌላ ትርጉም ያመጣል»ሲል ሁላችንም ከድንጋጤው ወጥተን ሳቅን፡፡
ስልኩን ሲጨርሱ ሁላችንም ወደርሳቸው መዞራችንን ሲያዩ ደንገጥ አሉ፡፡ አጠገባቸው ተቀምጠውየነበሩት አዛውንትም ፈገግ አሉላቸው፡፡
«ልጄ ልበልሽ ወይስ እናቴ?» አሉ አዛውንቱ በነጭ ሪዛቸው ውስጥ ፈገግታቸውን እያሳዩ፡፡
«ኧረ ልጄ ይበሉኝ» አሉ ተናደው የነበሩት ሴትዮ
«በጣም ጥሩ» አሉና አዛውንቱ ከወንበራቸው ላይ ተመቻቹ፡፡
«እይውልሽ በጣም ስትናደጅ እና በጣም ስትደሰች እባክሽ ውሳኔ አትወስኝ» አሏቸው፡፡ የሁላችንምጆሮ ወደ አዛውንቱ አቀና፡፡
«ቅድም እየተናገርሽ አልነበረምኮ፣ እየጮኽሽ ነበር፡፡ ጩኸት እና ንግግር ይለያያሉ፡፡ መናገርተረጋግቶ፣ አስቦ፣ ውጤቱን አስልቶ ነው፡፡ መጮኽ ግን አፍ እንዳመጣ ነው፡፡» አሏቸው፡፡
«አሁን ምን እንደተናገርሽ ብጠይቅሽ አታስታውሽውም፤ ምክንያቱም አንደበትሽ ሳይሆን ምላስሽ ብቻነበራ የሚናገረው»
«በአንደበት እና በምላስ መካከል ልዩነት አለ እንዴ» አለች አንዲት ወጣት፡፡ሌሎችም ራሳቸውንነቀነቁ፡፡
«ምላስ እና አንደበትማ ይለያያል፡፡ ምላስ ማለት ይቺ ቅልብልቢቱ ናት፡፡» አሉና ምላሳቸውንአውጥተው አቅለበለቧት፡፡ ሁላችንም ሳቅን፡፡ ሾፌሩ በተለይ ከልቡ ሲስቅ ጊዜ፡፡ «ሾፌር ይኼጨዋታ አንተን አይመለከትም ዝም ብለህ ንዳ» አሉት፡፡
«ይቺ እንዳ መጣላት የምትለፈልፈው ናት ምላስ፡፡ አንደበት ግን ልብ አውጥቶ አውርዶ ያቀበለውንለሰሚው የሚናገረው ነው፡፡ አንደበት ምላስን ይጨምራል፤ ምላስ ግን አንደበትን አይጨምርም»አሉ፡፡ ይኼ እኔ በሥነ ልሳን ከተማርኩት የተለየ ፍልስፍና ነው ብዬ መከታተል ቀጠልኩ፡፡
«ታድያ ሰው ሲናደድ ወይንም ሲደሰት ምንድን ነው ማድረግ ያለበት?» አላቸው አንደኛው፡፡
«ቢቻል ዝም ቢል መልካም ነው፤ »
«ካልቻለስ»
«ካልቻለ ደግሞ ውሳኔ የሌለው ነገር መናገር፡፡»
«ለምሳሌ ምን ዓይነት?»
«አየህ ልጄ እጅግ በጣም በተደሰትክ ጊዜ የምትወስነውን ቀርቶ የምትናገረውን አታውቀውም፡፡ስሜት መንፈስን ይጫነዋልና፡፡ ስሜት መንፈስን ከተጫነው ደግሞ ልቡና አይሠራም፡፡ በል በልአድርግ አድርግ የሚል ነው የሚመጣብህ፡፡ ስለዚህ ምንም አለመወሰን ነው፡፡ እነዚህ ገንዘብየሚሰበስቡ ሰዎች ምን እንደሚያደርጉ ታውቃላችሁ?» ብለው ሲጠይቁ አናውቅም በሚል ስሜትሁላችንም አየናቸው፡፡
«የሚያደርጉትኮ ሁላችንም እንድንደሰት ወይንም እንድናዝን ማድረግ ነው፡፡ ስሜታችንን መቀስቀስነው፡፡ ያን ጊዜ እኛ እጅግ በማዘንም ሆነ እጅግ በመደሰት ይህንን ያህል እንሰጣለን ብለን ቃልእንገባለን፡፡ ታድያ አንዳንዱ ሰው ስሜቱ ተረጋግቶ መንፈሱ ሲያንሠራራ ምን ነክቶኝ ነው ይላል፡፡ለዚህ ነው ስትደሰቱ ወይንም ስታዝኑ አትወስኑ ያልኳችሁ፡፡
«ግዴላችሁም አሳልፉት፡፡ ንዴት ዘላቂ አይደለም፡፡ ደስታም ጊዜያዊ ነው፡፡ ሰው አንድን ነገርከመናገሩ በፊት አምስት ነገሮች ያስፈልጉታል፡፡»
«ምን ምን» አልናቸው፡፡
«የቀደመ ዕውቀት፣ የቀደመ ልምድ፣ ያለበት ሁኔታ፣ የሚያመጣው ውጤት እና መፍትሔው መናገርነው ወይ?» የሚሉት ናቸው፡፡
«ይተንተኑ» አለ ሾፌሩ በንግግራቸው ተስቦ፡፡
«ስለምትናገረው ነገር ታውቃለህን? ወይስ እንዳመጣልህ ነው የምትናገረው? ይኼ ወሳኝ ነው፡፡አንተ ይህንን ለመናገር ዕውቀታዊ ሥልጣን አለህ? ይኼ መመለስ አለበት፡፡ ወዳጄ ስለማያውቁትነገር መናገርና ስለሚያውቁት ነገር ዝም ማለት አንድ ናቸው፡፡
«በዚያ ጉዳይ ላይ ከዚህ በፊት ልምድ አለህ? እንደዚያ ተናግረህ ነበር ካሁን ቀደም? ታድያ ምንገጠመህ? በሌሎች ሰዎችስ ምን ተማርክ? በጉዳዩ ላይ ምን ልምድ አለህ? ይህንን መልስ፡፡
«ለመሆኑ አሁን ያለህበት ሁኔታ ይህንን ነገር የሚያናግር ነው? እስኪ አስብበት፡፡ ታክሲ ውስጥ ነህ?አውቶቡስ ውስጥ ነህ? ቢሮ ነህ? ቤተ ክርስቲያን ነህ? ብቻህን ነህ? ከሰዎች ጋር ነህ? ደስ ብሎሃል?ከፍቶሃል? ርቦሃል? ጠግበሃል? ቸኩለሃል? ታምመሃል? ቸግሮሃል? ሁኔታህ ንግግርህን ይወስነዋል፡፡አሁን ቅድም እኅቴ የተናገረችው ነገር ታክሲ ውስጥ የሚነገር አይደለም፡፡ ከሰውዬው ጋር ለብቻማለቅ ያለበት ነው፡፡
«ሁኔታዎቹ ገፋፍተውኝ ነው የሚል ሰው አልሰማችሁም? ሊገፋፉትኮ ይችላሉ፡፡ ጥያቄው ለምንእርሱ በዚያ ሁኔታ ይናገራል? ልቡን የሚገፋው ሲያገኝ ከተናገረማ ጀርባውን የሚገፋው ሲያገኝ ገደልይገባል ማለት ነው፡፡ የሚገፋፋ ነገር ካለው ማቆም ነው፡፡
«መናገር ለውጤት መሆን አለበት፡፡ እገሌ ተናጋሪ ነው ለመባል፣ የንግግር ችሎታን ለማሳየት፣እንዴው መለፍለፍ አመል ስለሆነ፣ በሞቅታ ወይንም ተናግሮ አናጋሪ በመኖሩ መሆን የለበትም፡፡
«አስበን እንናገር፤ ወይንም ካላሰብን አንናገር፡፡ ምንም ሃሳብ ከሌለን ዝምታ ከንግግር በላይ ነው፡፡በእያንዳንዱ ንግግር መካከል የዝምታ ጊዜ ያስፈልጋል፡፡ የዝምታ ጊዜ ማለት የማሰቢያ ጊዜ ማለትነው፡፡ የታደሉት በአንደበታቸው ሲናገሩ በውስጣቸው ታላቅ ዝምታ አለ፡፡ ለማሰቢያ የሚሆንዝምታ፡፡
«ከበሮ በሚገባ ለምን ይጮኻል፡፡ የሚጮኽ እና የማይጮኽ ነገር ስላለው ነው፡፡ በከበሮው ግራ ቀኝየተወጠረው ቆዳ ይጮኻል፡፡ በከበሮው ዙርያ የተገጠመው እንጨት ደግሞ ዝም ይላል፡፡ የከበሮውድምጽ ከዝምታው መካከል ስለሚመነጭ ልዩ ነው፡፡ ሰውም ዝምታ እና ንግግር በአንድነትያስፈልጉታል፡፡
አረጋዊው ዝም አሉ፡፡ ምናልባትም እርሳቸው ራሳቸው ዝምታን ሊያሳዩን ይሆናል ብዬ አሰብኩ፡፡
«አምስተኛው ነጥብ ይቀራል» አለ ከጎናቸው የነበረ ተሳፋሪ
«ሞት ይርሳኝና ረሳሁት» አሉና ቀጠሉ፡፡ «አንዳንዱ ነገር በመናገር የማይፈታ አለ፡፡ ወይንምመፍትሔው መናገር ያልሆነ፡፡ ምናልባትም መፍትሔው ዝምታ ሊሆን ይችላል፡፡ ጸሎት ሊሆንይችላል፡፡ ወደ ሕግ መሄድ ሊሆን ይችላል፡፡ ለሚመለከተው ማመልከት ሊሆን ይችላል፡፡ ተግባርሊሆን ይችላል፡፡ ታድያ በመናገር ለማትፈታው ነገር ለምን በመናገር ትደክማለህ?»
«በሉ አንድ ታሪክ ነግሬያችሁ ልውረድ፤ እዚሁ ልታስቀሩኝኮ ነው፡፡» ፈገግ አሉ በነጩ ሪዛቸውመካከል፡፡
«በድሮ ጊዜ አንድ ሰው ጥፋት ያጠፋና ዳኛ ፊት ይቀርባል» ሁላችንም የተመካከርን ይመስል በአንድላይ «እሺ» አልናቸው፡፡
«ታድያ ዳኛው ሦስት ዓይነት የቅጣት ምርጫ አቀረቡለት፡፡ አንድ ኪሎ ሽንኩርት እየላጠ መብላት፣አንድ መቶ ጅራፍ መገረፍ፣ ወይንም አምስት መቶ ብር መክፈል፡፡ ሰውዬው ለማሰብ የሚሆን ልቡናየሌለው ነበርና የመጀመርያ ምርጫ ሆኖ ስላየው ብቻ «ሽንኩርቱን እበላለሁ» አላቸው፡፡
«ቀረበለት አንድ ኪሎ ሽንኩርት፡፡ ገና አንድ ሁለት መብላት ሲጀምር ዓይኑ ማልቀስ ለሐጩምመዝረብረብ ጀመረ፡፡ አልቻለም፡፡ ከመቀመጫው ተስፈንጥሮ ተነሣና፡፡
«መቶ ጅራፍ መገረፍ ይሻለኛል» አላቸው፡፡ ወዲያው ኃይለኛ ገራፊዎች ተጠሩና እየተፈራረቁይለበልቡት ጀመር፡፡ ግማሽ እንደደረሰ አልቻለም፡፡ እጁን ወደ ላይ አነሣ፡፡
«እህሳ» አሉት ዳኛው፡፡
«አልቻልኩም» አላቸው፡፡
«ታድያ ምን ይሻላል» አሉት እየሳቁ፡፡
«በቃ አምስት መቶ ብሩን እከፍላለሁ» አለ ከተኛበት እየተነሣ፡፡
«ያንተ ትልቁ ጥፋት መጀመርያ ወንጀል መሥራትህ ብቻ አይደለም፡፡ ማሰብ አለመቻልህ እንጂ፡፡ምናለ አስበህ ከሦስቱ አንዱን ብትመርጥ ኖሮ፡፡ እኔ ከሦስቱ አንዱን እንድትቀጣ ነበር የወሰንኩት፡፡አንተ ግን መናገር እንጂ ማሰብ ባለመቻልህ ሦስቱንም ተቀጣህ፡፡» አሉት፡፡
«ወዳጆቼ ሳያስቡ እንዳመጣ መናገር አንዱን ችግር ሦስት እጥፍ ያደርገዋል፡፡»
አሉና ወረዱ፡፡ አንዳንዶቻችን ወረድን፡፡ ሌሎች በታክሲው ቀጠሉ፡፡ አንዳንዶችም ከአረጋዊው ጋርከታክሲው በኋላም ጨዋታ ሳይቀጥሉ አይቀሩም፡፡ እኔ ግን የተናገሩትን ነበር የማመላልሰው፡፡
1 comments:
The Borgata Hotel Casino & Spa - DrMCD
Find out more about The Borgata Hotel Casino & Spa - 성남 출장안마 DrMCD. The 고양 출장안마 Borgata Hotel Casino & Spa, located 오산 출장마사지 in Atlantic City, New Jersey, 보령 출장마사지 features 태백 출장샵
Post a Comment