Check out changes at Finote Selam

Check out the new Finote Selam after being A capital city of W/Gojjam zone early this year.

Finote Selam new Music

new music by solomon demle .

public library in Finote Selam

time to support our people.

Finote Selam

time to support our people.

Thanks for Visiting

Sunday, September 23, 2012

Teddy Afro New Wedding Song - Yemushiraye Enat


Tuesday, September 4, 2012

የተማርንበትም የተማረርንበትም ሰሞን



(ፎቶው የቢቢሲ ነው)
የጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ሞት ከተረዳበት ሰዓት ጀምሮ ሀገራችን አዲስ መልክ ይዛለች፡፡ ያለፉት ቀናት ስለራሳችን የተማርንባቸው፤ በራሳችንም የተማረርንባቸው ቀናት ነበሩ፡፡ እስኪ ከተማርንባቸው ልጀምር፡፡
ትዝ ይለኛል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ከውጭ ሀገር ወደ አዲስ አበባ የሚገቡበት ጊዜ ነበር፡፡ በቦሌ ጎዳና ፖሊሶች አዚህም እዚያም በዛ ብለዋል፡፡ እኔ ደግሞ አልሰማሁም ነበርና እዚያ አካባቢ ለሥራ መሄድ፡፡ ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ መንገዱ ጭር አለ፡፡ ፖሊሶችም መጡና ከአካባቢው ዘወር እንድንል ነገሩን፡፡ የሚገርመው ነገር ግን አካባቢው በአፓርታማዎች የተጠቀጠቀ ነበርና ዘወር የምንልበት ቦታ ጠፋን፡፡ ፖሊሱ ግን አሁንም አሁንም ከአካባቢው ዘወር እንል ዘንድ ያዝዛል፡፡ ግን የት ዘወር እንበል? በመጨረሻ መጣና በአፓርታማው የታችኛው ክፍል ካሉት ቤቶች አንዱን አንኳኳ፡፡ አንዲት በእድሜ ጠና ያሉ ሴት ከፈቱ፡፡ ‹‹ግቡ›› አለን ፖሊሱ፡፡ አንድ ሰባት እንሆናለን፡፡ ግራ ገብቶን ተያየን፡፡ ከጀርባችን ገፋ ገፋ እያደረገ ሰው ቤት ውስጥ አስገባን፡፡ ስለ ቻይና ባቡርና ፖሊስ ያየሁት ፊልም ነው ትዝ ያለኝ፡፡ ሴትዮዋ በሩን እንዲዘጉ ተነገራቸው፡፡ ተዘጋ፡፡
አሁንም ሰው ቤት ገብተን ተያየን፡፡ ደግነቱ ሴትዮዋ ተግባቢ ናቸውና ‹‹በሉ እንግዲህ መንግሥት ካዛመደን ዐረፍ በሉና ሻሂ ጠጡ›› አሉን፡፡ እኛም ሳቅ እያልን ባገኘነው ወንበር ተቀመጥን፡፡ እዚያ ተቀምጠንም በባለ ሥልጣኖቻችንና በሕዝባቸው መካከል ስላለው ግንኙነት ተቸን፤ አማን፤ ሃሳብም ሰነዘርን፡፡ ከዚህ በፊት ያጋጠመንንም ተጨዋወትን፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትሩ አስከሬን በመጣበት ማታ ይህንን አጋጣሚ ነበር የማስበው፡፡ ሕዝቡ ግልብጥ ብሎ መንገድ ላይ ወጥቶ ነበር፡፡ በአንዳንድ አደረጃጀቶች በኩል ከመጡ ጥቂት ሰዎች በቀር አብዛኛው ሰው በራሱ ፈቃድ ኀዘኑን ለመግለጥ ታሪክም ለማየት ነበር የወጣው፡፡ ጧፍ እንኳን ያበራው ዕለቱ የፍልሰታ ጾም ማብቂያ የኪዳነ ምሕረት ዋዜማ በመሆኑ በቦሌ መድኃኔዓለም፤ በኡራኤል፣ በእስጢፋኖስና በግቢ ገብርኤል አካባቢ ለበዓሉ ጧፍ ለመሸጥ ከተቀመጡት እናቶች እየገዛ ነበር፡፡ ጧፍ ማብራትን ሕዝቡ ራሱ ያመጣው የአቀባበል ሥርዓት ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ ግን በየ ቀበሌው ተዳረሰ፡፡
ያን ምሽት ሕዝቡ ወደ ቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ በሰላምና ያለ አንዳች ችግር ሲገባ ነበር፡፡ ከፖሊስ ጋር ግርግር የፈጠረ አልነበረም፡፡ ጨዋነት ጎልታ የወጣችበት ምሽት ነበር፡፡ በመንገድም ላይ ቢሆን የነበረው ሁኔታ አስቀድሞ ያልተገመተው የሕዝቡ ማዕበል ከተጠበቀው በላይ መሆኑ ነበር፡፡ የጸጥታ አስከባሪዎች መጀመርያ ላይ አስከሬኑ ከሕዝብ ርቆ ግራና ቀኝም ተከልሎ እንዲያልፍ አስበው ነበር፡፡ ሕዝቡ ግን ፈቃደኛ አልሆነም፡፡ እያለቀሰና እየተከዘ አብሮ መጓዝን መረጠ፡፡ ነገሩንም ሲረዱት እነርሱም ተውት፡፡ እንዲያ ዝናብ እየቀጠቀጠው፤ እንዲያ ብርድ እያንቀጠቀጠው የዐሥር ደቂቃ መንገድ አራት ሰዓት እስኪፈጅ ድረስ አስከሬኑን በክብር አጅቦ፤ ራሱ ባወጣው ሥርዓትና አሠራር ተጓዘ፡፡ ምንም ዓይነት የጸጥታ ችግር ሳይፈጠር አስከሬኑ ቤተ መንግሥት ደረሰ፡፡
ለመሆኑ ከዚህ መማር የለብንም?
የኢትዮጵያ ሕዝብ ጨዋ ሕዝብ ነው ስንል ምን ማለታችን ነው?
ይህ ሕዝብ መሪዎች ወይም ባለ ሥልጣናት ባለፉ ባገደሙ ቁጥር ሊንገላታ የማይገባው ሕዝብ ነው ማለት ነው፡፡ ይህ ሕዝብ ሊከበር እንጂ ሊሰጋ የማይገባው ሕዝብ ነው ማለት ነው፡፡ ይህ ሕዝብ ቀርበው ሊያወያዩት፤ ችግሩን በቅርብ ሊያዩለት የሚገባ ሕዝብ ነው ማለት ነው፡፡ ይህ ሕዝብ ወደ ሀገሪቱ ከሚመጡ እንግዶች በላይ ሊከበር የሚገባው ሕዝብ ነው ማለታችን ነው፡፡ ይህ ሕዝብ ቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ ተገኝቶ ዘመዱን ለመቀበል አትገባም ውጭ ቆመህ ዝናብ ይቀጥቅጥህ ሊባል የማይገባው ሕዝብ ነው ማለት ነው፡፡ ይህ ሕዝብ ፍትሕ ለማግኘት ዓመት ሁለት ዓመት ሊጉላላ የማይገባው ሕዝብ ነው ማለት ነው፡፡ ይህ ሕዝብ በጎ ለሚሠሩ ሁሉ ስሕተታቸውንና ጥፋታቸውን እያወቀ እንኳን የሚደግፍ ነውና ሊያሳዝኑትና ሊያቀስቀይሙት የማይገባ ሕዝብ ነው ማለት ነው፡፡ ይህ ሕዝብ ኮንደሚንየም ብርቅ ሊሆንበት የመይገባ ሕዝብ ነው ማለት ነው፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ለመጀመርያ ጊዜ በሕዝብ ታጅበው ቤተ መንግሥት ሲገቡ አየሁ፡፡ ምናለ በሕይወት በነበሩ ጊዜ ይህ ሆኖ በነበረ፡፡ ይኼው ሕዝብ ነውኮ ያኔም የነበረው፤ ይኼው ጨዋ ሕዝብ እኮ ነው የሚያጅባቸው፤ ይኼው ጨዋ ሕዝብ እኮ ነው የሚጠይቃቸው፤ የሚያወያያቸው፡፡ ይህ ሕዝብኮ እዚሁ የነበረ ነው፡፡ ከአውሮፓ ወይም ከእስያ አልመጣም፡፡ ቀጣዮቹም ባለሥልጣናት ይህንን ትምህርት መውሰድ አለባቸው፡፡ ባለ ሥልጣናት ሆይ ሰው ሁኑ፡፡ ሰው ያልሆነው አምላክ እንኳን ሰው ሆኖ በሰው ቋንቋ ተነጋግሯል፡፡ ከሰው ጋር ውሎ አድሯል፤ ከሰው ጋር በልቷል፡፡ ከሰው ጋር ተጉዟል፡፡ እናንተ ታድያ ሰው ብትሆኑና ከሰው ጋር ብትኖሩ ምናለበት? እርሱ አምላካችን ሰው ሆኖ የሰውን መከራ፣ ስቃይና ኀዘን ቀምሶታል፡፡ እናንተስ ሰው ሆናችሁ መከራችንን፣ ችግራችንንና ኀዘናችንን ብትቀምሱት ምናለ? እስከ መቼ በሪፖርትና በስብሰባ ብቻ እንገናኛለን? እስከ መቼ በቴሌቭዥን ብቻ እንተያያለን?
ሪፖርት ቢጽፉት እንደ አካል አይሆንም
ቴሌቭዥን ቢያዩት እንደ አካል አይሆንም
ስብሰባ ቢጠሩት እንደ አካል አይሆንም
እንገናኝና ልናገር ሁሉንም
ተብሎ መዘፈኑን አልሰማችሁም?
በጠቅላይ ሚኒስትሩ ሞት ቤተ መንግሥት ተከፈተ፡፡ ይህ ደግሞ አቶ መለስ የሠሩት ሌላው ታሪክ ነው፡፡ እኔ ስለዚህ ቤተ መንግሥት ክፉ እንጂ ደግ ሰምቼ አላውቅም ነበር፡፡ በተለይ በደርግ ዘመን ስለነበረው ሁኔታ የተጻፉት ሁሉ ስለዚያ ቤተ መንግሥት የሆረር ፊልም ያህል ሲያስፈራሩን ነበር፡፡ ምናልባት ሕዝብ በብዛት ሆኖ ወደዚያ ቤተ መንግሥት የገባው በንጉሡ ጊዜ ግብር ለመብላት ሳይሆን አይቀርም፡፡ እርሱንም ሰምተን እንጂ አላየንም፡፡ ከዚያ ወዲያ ባለፉት ዓርባ ዓመታት ለሕዝብ የተከለከለ ቦታ ነበር፡፡ እንዴው አልፎ አልፎ ከተለያዩ አካላት ጋር ውይይት ካልኖረ በቀር ቤተ መንግሥቱና ሕዝቡ በማኅበራዊ ነገር አልተገናኝተውም ነበር፡፡
(ፎቶው የቢቢሲ ነው)
እነሆ ሕዝብ ተሰለፈና ቤተ መንግሥት ገባ፡፡ ይህንንም ቢሆን ሕዝብ የፈጠረው ይመስለኛል፡፡ የአቶ መለስ ሞት ከተረዳበት ሰዓት ጀምሮ ሚዲያዎቹን ያጨናነቀው ጥያቄ የት ሄደን ልቅሶ እንድረስ? የሚለው ነበር፡፡ የቀብር አስፈጻሚው ብሔራዊ ኮሚቴም ለዚህ በጎ ምላሽ በመስጠቱ ይመሰገናል፡፡ ወደ ቤተ መንግሥት እንደሚገባ በቀበሌም በአደረጃጀትም፣ በሚዲያም ከመነገሩ በፊት ነበር ሕዝብ ቤተ መንግሥቱን ያጥለቀለቀው፡፡ [እዚህም ላይ ሌላ አስመራሪ ነገር ገጥሞን ነበር፡፡ በሀገር ውስጥ ያሉት የመንግሥት ሚዲያዎች ሰው ግልብጥ ብሎ የወጣው የጠቅላይ ሚኒስትሩን ፖሊሲና ስትራቴጂ ሙሉ በሙሉ በመቀበሉና በመጠቀሙ ነው ይሉ ነበር፡፡ የውጮቹ ደግሞ ተገድዶና ተደልሎ ነው፤ አደርባይ ስለሆነም ነው ይላሉ፡፡ የሁለቱም ችግር ሕዝብን ካለ ማወቅና ለራሱ ጥቅም ሁሉንም ነገር ከመጎተት የመጣ ነው፡፡
አስከሬኑ አዲስ አበባ ሲገባም ሆነ በቤተ መንግሥቱና በየአካባቢው በተከናወነው ልቅሶ ሕዝቡ በፖሊሲዎችና በስትራቴጂዎች ሙሉ በሙሉ ተስማምቶ ብቻ የወጣ አይደለም፡፡ ምክንያቱ ልዩ ልዩ ነው፡፡ በርዕዮተ ዓለማቸውና በሥራቸው ተደስቶ ነገር ግን በሆነው ነገር አዝኖ የወጣ አለ፡፡ በአንዳንድ ሃሳባቸው ተስማምቶ በሌላው ተለያይቶ በመሞታቸው ግን አዝኖ የወጣ አለ፡፡ በእርሳቸው አስተሳሰብም ሆነ ሥራ ምንም ሳይስማማ፣ ነገር ግን የሀገሩ መሪ በመሞታቸው አዝኖ የወጣም አለ፡፡ ታሪክ ለማየት ሲልም የወጣም አለ፡፡ እርሳቸውን እየተቃወመም በባሕሉ ልቅሶ መድረስ አለብኝ ብሎ የወጣም አለ፡፡ ይህ ሁሉ እኛን ይደግፋል ብሎ ማሰብና በዚህ ተመሥርቶ ውሳኔ መወሰን ከስሕተት ይጥላል፡፡
ይህ ሕዝብ ተገድዶ የወጣ አድር ባይ ነው ብሎ ማሰብም ሌላው ስሕተት ነው፡፡ ምናልባት እንዲያውም አብዛኛው ኀዘኑን በባህሉ መሠረት ለመግለጥ የወጣ ነው፡፡ ጥቂት ሊገደዱ የሚችሉ ይኖራሉ፤ ታይተዋልም፡፡ ውጡ ብለው መመርያ ለማውጣት የሞከሩ ታናናሽ ባለ ሥልጣናትም ነበሩ፡፡ ሕዝቡ ግን የተጓዘው በራሱ ነው፡፡ መቼም ሕዝብን በግድ ማሰለፍና አደባባይ ማውጣት ይቻል ይሆናል እንጂ እንዲያለቅስ፣ እንዲደነግጥ፣ ፌንት እንዲያደርግ፤ መሬት እንዲንከባለል ማድረግ የሚቻል አይመስለኝም፡፡ በርግጥ ለደረት ድቂያ፣ ለአስለቀሽና ለእድር ድንኳን አንዳንድ ቅመማ ቅመም ሳይጨመርበት አይቀርም፡፡ ሁሉንም በአንድ ፋይል ጠቅልሎ ተታልሎ ነው፣ ተገድዶ ነው፣ አድር ባይ ሆኖ ነው ማለት ግን የኢትዮጵያን ሕዝብ አለመረዳትን የሚያሳብቅና ወደ ተሳሳተ ውሳኔም የሚያደርስ ነው፡፡]
ሕዝቡ ባህላዊ ሕዝብ ነው፡፡ አዛኝ ሕዝብም ነው፡፡ ያዘነበት የየራሱ ምክንያት አለው፡፡ አንድ ያደረገው ማዘኑ ነው፡፡ ራሳቸውን የሚስቱ፤ የሚያደርጉትን የማያውቁ፤ እየሆነ ያለውን ነገር መቀበል ያቃታቸው፤ የነገሮች መገጣ ጠም ያስደነገጣቸው፤ መሪ ሲሞት፤ ሲለቀስለትም አይተው ባለማወቃቸው ግራ የገባቸው ሰዎች ነበሩ፡፡ ሁሉም ግን አዝነው ነበር፡፡ ሕፃናት፣ ወጣቶች፣ ዐዋቂዎች፣ አረጋውያን፤ የተማሩ፣ የከተማ የገጠር ሁሉም ወደ አራት ሰዓታት የፈጀ ሰልፍ ይዘው ኀዘናቸውን ለመግለጥ ገብተዋል፡፡[እዚህ ላይ ግን ሌላ የሚያስመርር ነገር ነበር፡፡ ሕዝብ አዝኗል፡፡ ኀዘኑን የሚገልጥበት ቦታም ይፈልጋል፡፡ በባሕላችን ኀዘናችንን የምንገልጥበት ቦታ እንፈልጋለን፤ እገሌ ሞተ ሲባል ልቅሶ የሚደረሰው የት ነው? መባሉ የተለመደ ነው፡፡ አንዳንድ እወደድ ባዮች ግን ልቅሶውንና ወደ ቤተ መንግሥት መሄዱን እንደ ግዴታ ለማድረግ ሞክረዋል፡፡ ለምን? ይህ ከማማረር በቀር ምን ፋይዳ ይሰጣል? ወይስ እኛ ያልሠራነው ሥራ እንደ ተሠራ አይቆጠርም? በመጨረሻዎቹ ሦስት ቀናት በተደረገው የስንብት መርሐ ግብር ጊዜ በየአካባቢው የታየው አስገዳጅ የመሰለ ቅስቀሳ የሕዝቡን ስሜት ወደ መረበሽ ተሻግሮ ነበር፡፡ ፈጽሞ መደገም የሌለበት አስመራሪ አሠራር አንዱ ይኼ ነው፡፡]
ምንም እንኳን የሕዝቡ ቁጥር ከተጠበቀው በላይ ቢሆንም፤ ምንም ያህል ያልታሰበ ቢሆን ሕዝቡን ለማስተናገድና ሕዝቡም እንዳይቸገር ለማድረግ የጸጥታ አስከባሪዎች ያደርጉት የነበረው ጥረት ሊደነቅ ይገባዋል፡፡ የማመናጨቅ፤ የመሳደብ፤ የመገፍተር፣ አይቻልም አይቻልም ብሎ የመዝጋት ጠባይ አይታይም ነበር፡፡ መጀመርያ በአንድ በር ፤ በኋላም በሁለት በር፤ ከዚያም በዋናው በር በኩል በማስገባት በመስተንግዶ ሠልጥነዋል ከሚባሉት ከሆቴል አስተናጋጆች እንኳን በማይገኝ ትኅትናና ቅልጥፍና ለማስተናገድ ጥረዋል፡፡
እኔ ይህንንም ነገር ነው እንማርበትና እንቀጥል የምለው፡፡ ድሮ ድሮ ሌባና ፖሊስ ስንጫወት ፖሊስ አባራሪ ሌባ ተባራሪ ይሆን ነበር፡፡ ይህ ጨዋታ ሌባ በሌለበትም ሳይቀጥል አልቀረም፡፡ ሕዝብና ፖሊስ ተከባብሮ እንጂ ተፈራርቶ መኖር የለበትም፡፡ ፖሊስ ሕዝቡን የሚያገለግል፤ ለሕዝቡም ጸጥታ የሚተጋ መሆኑን ማስመስከር አለበት፡፡ ፖሊስን ወንጀለኛ ብቻ እንዲፈራው መደረግ አለበት፡፡ ‹‹ፖሊስ እጠራብሃለሁ›› እያሉ ልጆችን ማስፈራራት እንዲቀር ፖሊሶቹ ራሳቸው መሥራት አለባቸው፡፡
ይህ የአሁኑ ትውልድ ቤተ መንግሥት ምን እንደሚመስል፤ የሚመራው ሰው የት እንደሚሠራ፤ የት እንደሚኖር ለመጀመርያ ጊዜ ያየበት ዕድል ነው የገጠመው፡፡ እንዲያውም አንዳንዶች የጠቅላይ ሚኒስትሩን ቢሮና ቤት አይተው ተገርመዋል፡፡ እንደዚያ እንደማይመስላቸው ይናገሩ ነበር፡፡ ካሰቡት በታች ሆኖባቸው ‹‹እኒህ ሰው እዚህ ነበር እንዴ የሚኖሩት?›› ብለዋል፡፡ ለምን ግን የራሳችንን ቤተ መንግሥት በሕልም ብቻ እንድናየው ተደረገ? ለምንድን ነው ስለ መሪዎቻችን ብዙ ነገር እንዳናውቅ የሚደረገው? ብናውቅ ምን ይሆናል? ያኔስ ቢሆን አሁን ያወቅነውን አልነበር የምናውቀው? ምን የተለየ ነገር ነበረው?
ስለ አቶ መለስ ጠባያት፣ የሥራ ሁኔታ፤ ትጋትና ማንነት በሕይወታቸው እያሉ ከምናውቀው በላይ አሁን ነው የሰማነው፡፡ መስማታችን እሰየው፡፡ ግን ይህንን ቀደም ብሎ መስማት አይቻልም ነበር? በርግጥ እርሳቸው ስለ ራሳቸው መናገርም ሲነገር መስማትም ብዙም አይፈልጉም ነበር ይባላል፡፡ የርሳቸው አለመፈለግ መልካም፡፡ ግንኮ መሪ የሚፈልገውን ብቻ አይሠራም፤ ሕዝብ የሚያስፈልገውንም ጭምር እንጂ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ማለት ግለሰብነት ብቻ አይደለም፡፡ ሕዝባዊ አካልም ነው፡፡ ሕዝብ ስለ መሪው ማወቅ አለበት፡፡ ሊነገረው ይገባል፡፡ ስለ መሪው የማያውቅ ሕዝብ ሁለት ነገር ይገጥመዋል፡፡ ወይ ባለ ማወቅ መሪውን ይቃወመዋል፤ ወይም ባለ ማወቅ መሪውን ይደግፈዋል፡፡ ሁለቱም ግን አደገኞች ናቸው፡፡ ባለማወቅ የደገፈም ሲያውቅ ይሸሻል፤ ባለማወቅ የተቃወመም ሲያወቅ ይፀፀታል፡፡
ከሁሉም በላይ የተደነቅኩት ግን በቀብሩ ዕለት ነው፡፡ በሕይወቴ ይሆናል ብዬ ከማላስባቸው ነገሮች አንዱ የሆነውም ትናንት ነው፡፡ አንድ ወዳጄ ማታ ስደውልለት ‹‹በጠቅላይ ሚኒስትሩ ቤት ጸሎተ ፍትሐት ልናደርግ መሄዳችን ነው›› አለኝ፤ አላመንኩትም፡፡ ሰዓቱ ከምሽቱ ወደ ሦስት ሰዓት ሆኖ ነበር፡፡ ካህናቱ፣ ዲያቆናቱ፣ መሪጌቶቹ ተሟልተው ሙሉ ጸሎት ሲደረግ ነበር ያደረው፡፡ የቤተ መንግሥቱ ሰዎች ለጸሎቱ የነበራቸው ክብርና ሥነ ሥርዓት የሚገርም ነበር፡፡
ከዚያም የኢትዮጵያ ቴሌቭዥን የመጨረሻውን የጸሎት ሥነ ሥርዓት አሳየን [ግን ጋዜጠኞቹ ምን ነክቷቸው ነው? ሃይማኖታዊ ጸሎት ሲሉ የዋሉት፡፡ ለመሆኑ ሃይማኖታዊ ያልሆነ ጸሎት አለ? ‹ፍትሐት› የሚለው ቃል ጠፍቷቸው ነው? የቻይናው ቴሌቭዥን እንኳን ያወቀውን ቃል እነርሱ ምነው ጠፋቸው? ይባስ ብለው በቅድስት ሥላሴ ካቴድራል የነበረውን ጸሎት ‹ቅዳሴ› እያሉ ይጠሩት ነበር፡፡ ለነገሩማ ‹በቅድስት ሥላሴ ካቴድራል› ለማለት ‹በቅድስት ካቴድራል ሥላሴ› ይሉ እንደነበር ስሰማ ይቅር ብያቸዋለሁ፡፡ ኧረ እንዲያውም የዛሬው ልቅሶ የሚያምር ልቅሶ ነው ያለን ጋዜጠኛም ነበር፡፡
 ሚዲያዎቻችን ከልምድ ማነስም ሊሆን ይችላ የችግርንና የኀዘንን ወቅት እንዴት መዘገብ እንደሚቻል መማር አለባቸው፡፡ ሁለት ሳምንት ሙሉ የፍቅር እስከ መቃብርን ዋሽንት ብቻ ከማሰማት የተለያዩ ፕሮግራሞችን ማዘጋጀት አይቻልም ነበር? ስለ አቶ መለስ ማንነት የሚያውቋቸውን ማነጋገር፤ የውይይት መርሐ ግብር ማዘጋጀት፤ ሌላም ሌላም አይቻልም ነበር? የቃለ መጠይቅ ጥያቅዎቹስ ለሕፃኑም፣ ለዐዋቂውም፣ ለተማረውም፣ ለማይሙም አንድዓይነት መሆን አለባቸው? ራሳቸው ጋዜጠኛ ራሳቸው ተንታኝ እንዲሆኑስ የቱ አሠራር ነው የፈቀደው? አንዳንዴ እንዲያውም  ስብከትም ሁሉ ይመስል ነበር? ደግሞስ ሰው አኳሽቶና አጋንኖ የሚናገረውን ነገር ሁሉ ማቅረብ አለባችሁ? ጋዜጠኞቻችንኮ ስለ አቶ መለስ ሁሉን ዐዋቂ ሆኑብን፤ ቢያንስ አብረዋቸው የተጓዙት፤ አብረዋቸው የሠሩት፤ አብረዋቸው የኖሩት፤ ስለ እርሳቸው የጻፉት ቀርበው ቢነግሩን ምናለ? ይቺ አሠራር ታስመርራለችና መታረም አለባት]፡፡
ወደ መስቀል አደባባይ የተጓዘውም ከፊትና ከኋላ ድባብ በያዙ ካህናት፣ ማዕጠንት በያዙም ጳጳሳት ታጅቦ ነበር፡፡ ይቅርታ ይደረግልኝና ካለፈው ጊዜ ይልቅ የፓትርያርኩ ቀብር የመሰለን ይኼኛው ነው፡፡ የጉዞው ሥነ ሥርዓት አዘጋጆቹንም ሆነ አከናዋኞቹን ያስመሰገነ ነበር፡፡ እመለስበታለሁ፡፡
በመስቀል አደባባይ መርሐ ግብሩ በጸሎት መጀመሩን ሳይ ዓይኔ ነው ወይስ ቴሌቭዥኑ ነው? አሰኝቶኛል፡፡ ይህ እንዲሆን ያደረገ ማነው? የአቶ መለስ ኑዛዜ? የወይዘሮ አዜብ ፍላጎት? ወይስ የመንግሥት ፈቃድ? ከወሬ ባለፈ መረጃ ባውቀው እንዴት በወደድኩ፡፡ መቼም ሰው ሆኖ ከሥላሴ ቤት የሚቀር የለምና የአቶ መለስ አስከሬን ወደ ቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን ሲገባ የነበረውን ሥነ ሥርዓት ምነው ከሳምንት በፊት ልናየው አልቻልንም አሰኝቶኛል፡፡
አስከሬኑ በቤተ ክርስቲያን ሥርዓት መሠረት ቤተ መቅደሱን ዞሮ ነው ወደ መቃብሩ የገባው፡፡ ባለፈው ጊዜ ይህንን አላየሁምሳ? የካህናቱ ወረብ፣ የሰንበት ተማሪዎቹ መዝሙር፣ የአቡነ ናትናኤልና የአቡነ አረጋዊ ትምህርት ‹‹እውነት ለአቶ መለስ ነው ይህ የሚደረገው?›› አስብሎኛል፡፡ መለስ ከሕይወታቸው ይልቅ[በሕይወታቸው የሠሩትን እንዲህ በሚታይና በሚሰማ ደረጃ ስለማላውቅ] በሞታቸው ቤተ ክርስቲያንን ከፍ ከፍ አድርገዋታል፡፡
ይህቺ ቤተ ክርስቲያን ምን ያህል ክብርና ሞገስ እንደምትሆን ተተኪዎችም ትምህርት ይወስዳሉ ብዬ አስባለሁ፡፡
መሪ በመፈንቅለ መንግሥት ሳይገለበጥ፤ በጦርነት ተሸንፎ አገር ጥሎ ሳይወጣ፤ በአብዮት ከዙፋን ወርዶ እሥር ቤት ሳይገባ በተፈጥሮ ሞቶ በክብር ሲቀበር ለእኔ ትውልድ አዲስ ታሪክ ነው፡፡ የኔ ትውልድ ስለ መሪው ስደትና ሞት ሲሰማ እንጂ መሪውን አልቅሶ ሲቀብር አላየሁም፡፡ መለስ በዚህ ታሪክ ሠርተዋል፡፡
ከቤተ መንግሥት እስከ መስቀል አደባባይ፤ ከመስቀል አደባባይ እስከ ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል የነበረው ሥነ ሥርዓት አዘጋጆቹንም፣ ተሳታፊዎቹንም የሚያስመሰግን ነበር፡፡ የፕሮግራሙ በተያዘለት ሰዓት ማለቅ፡፡ በተለይም አቶ ኩማ ደቅሳ እንኳንም መድረኩን ለ‹‹አርቲስቶች›› አልሰጡብን ብያቸዋለሁ፡፡ እንዲህ እጥር ምጥን አድርገው አይመሩልንም ነበር፡፡ [በዚሁ ግን አንድ አስመራ ነገር መናገር ያስፈልጋል፡፡ ሰሞኑን ይወጡ የነበሩ ግጥሞች ከታገል ሰይፉ ግጥም በቀር ሚዛን የሚደፋ አጣሁ፡፡ ትትትትትት፣ንንንንንን፣ ችችችችችች፣ ምምምምምም ብቻ የተደረደረባቸው ናቸው፡፡ አንባቢዎችም ለመድረኩ የማይመጥኑ፣ ግጥሙንም ወደ ስድ ንባብ በመቀየር የተካኑ ናቸው፡፡ ከተዘፈኑትም መካከል ከአንዱ በቀር የግጥም ለዛ ያለው የለም፡፡ ምነው ለቸበር ቻቻ እንጂ ለኀዘን የሚሆን ግጥም አጣንሳ]
ያ እንደ ደዶፍ የወረደው ዝናብ ሥነ ሥርዓቱን ሳያሰናክለው፡፡ ከፖሊሶቹና ከወታደሮቹ ቆብ ላይ ዝናቡ እንደ ጣራ ፍሳሽ እየወረደ ሥነ ሥርዓቱ ግን ቀጠለ፡፡ መንገዱ ሁሉ ጎርፍ ነበረ፡፡ ተጓዦቹ ግን ችግሩ ሳይፈታቸው እነርሱም ጨዋነታቸውን አሳይተዋል፡፡ በቤተ ክርስቲያኑ የነበረው ሥነ ሥርዓትም በተያዘው ሰዓት የተከናወነና ለዓይን የማይጎረብጥ ነበር፡፡ አቶ መለስ ተነሥተው የሰሞኑን ሁኔታ ቢያዩ በአንዳንዱ ነገር የሚገረሙና የሚደነቁ፤ በአንዳንዱ ነገር የሚያዝኑና የሚቆጩ፣ በአንዳንዱም ነገራችን የሚናደዱ ይመስለኛል፡፡
በዚያም ተባለ በዚህ ግን አቶ መለስ በሞታቸው ታሪክ ሠሩ፤ እኛም በሳቸው ሞት ታሪክ አየን፡፡ 
Source Daniel Kibret's view 

Twitter Delicious Facebook Digg Stumbleupon Favorites More